· የመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ጽ/ቤት አይመለከተውም ተብሎ ተሰናብቷል
· የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ልማት ድርጅቱ እና ተከራዮቹ ከሆቴሉ ዞር እንዲሉ ተነግሯቸዋል
· ፓትርያርኩን የአስተዳዳሪው ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ አሜሪካ ጉዞ ጥርጣሬ ላይ ጥሏቸዋል
· በአስተዳዳሪው ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ ላይ መዛታቸውም ተሰምቷል፡፡
· ደብሩ ተከራዮቹን አስወጥቶ ሆቴሉን ተረክቧል
(ኖላዊ ዘተዋሕዶ፤ታህሳስ 1 ፤2004)፡- የግርማዊ ቀዳማዊ ዐጼ ኀይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ የሆኑት ልዕልት ኂሩት ደስታ“ለቅዱስ ላሊበላ ደብር መርጃ ይሁን” በሚል በስጦታ ያበረከቱት የ‹‹ሰባት ወይራ ሆቴል ባለቤት››የቅዱስ ላሊበላ ደብር መሆኑ በፍርድ ቤት ተረጋገጠ፡፡
የጉዳዩ መነሻ
የግርማዊ ቀዳማዊ ዐጼ ኀይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ የሆኑት ልዕልት ኂሩት ደስታ በ1963 ዓ.ም “ለቅዱስ ላሊበላ ደብር መርጃ ይሁን” በማለት ደብሩ ሆቴሉን በባለቤትነት ይዞ እያስተዳደረ ገቢው ለማስቀደሻ እና ለጧፍ እንዲጠቀምበት በማሰብ የ‹‹ሰባት ወይራ ሆቴል››ን በጹሑፍ ይሰጣሉ፡፡ ገዳሙ ስጦታውን ከተቀበለ አራት ድፍን ዓመታት እንኳን በቅጡ ሳይቆጠር በደርግ የሥልጣን ዘመን ከተወረሱት በርካታ ቤቶች መካከል አንዱ ሆነና በጊዮን ሆቴሎች አስተዳደር ድርጅት እጅ ወደቀ፡፡ኢሕአዴግ የመንግሥትነቱን ሥልጣን ከተረከበ በኋላ በ1991 ዓ.ም ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ለጠቅላይ ቤተክነት ‹‹ሰባት ወይራ›› የተባለው ሆቴል ንብረትነቱ የቅዱስ ላሊበላ ገዳም መሆኑ ስለተረጋገጠ፣ እንዲረከቡ የሚጠይቅ ደብዳቤ ይጽፋል፡፡ቤተክህነቱም ደብዳቤውን መነሻ በማድረግ ገዳሙ ሆቴሉን ለመረከብ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርግ ለደብሩ በደብዳቤ ያስታውቃል፡፡እነዚህ ደብዳቤዎች ከተጻጻፉ ከሰባት ዓመት በኋላ፣ በ1997 ዓ.ም ከገዳሙ እውቅና ውጪ በግዮን ሆቴሎች እና በጠቅላይ መካከል ርክክብ ይፈጸማል፡፡
ቤተክህነቱ
የገዳሙን የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ሆቴሉ ለገዳሙ የተበረከተ ስጦታ መሆኑን በመግለጽ ሆቴሉ ለደብሩ እንዲመለስ ቢጠይቁም ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሆቴሉን እንደ ሌሎቹ የተወረሱ የቤተክርስቲያኒቱ ቤቶች ከመንግሥት ጋር በተደረገ ልዩ ስምምነት ያስመለሰችው በመሆኑ፣ ንብረትነቱ የእርሷ እንጂ የገዳሙ ሊሆን እንደማይገባ በመግለጽ ሆቴሉም መተዳደር ያለበት በጠቅላይ ቤተክህነቱ ሥር ነው ስትል ክርክር ታቀርባለች፡፡በዚህም መሰረት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የቤቶችና ሕንጻዎች አስመላሽ ኮሚቴ ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ተረክቦ ለሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት፣ ሀገረ ስብከቱም ለደብሩ ሊሰጥ ስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡