· ምእመኑ በየተራ ቤተክርስቲያኒቱን ሲጠብቅ ነው የሚያድረው
· አቤተታቸውን ለፓትርያርኩ አቀረቡ
· ፓትርያርኩ አጣሪ ኮሚቴ ይሾማል ብለዋቸዋል
(ኖላዊ ዘተዋሕዶ፤ታህሳስ 7 ፤2004)፡- ቀደም ሲል በቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን ላይ ምዝበራን ሲያካሂዱ በመገኘታቸው እንዲነሱ የተደረጉት አባ ዕዝራ ተክለ ጊዮርጊስ አሁን ደግሞ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል (አዲሱ ሚካኤል) ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ቤተክርስቲያኒቱን እየመዘበሩ እና ከአንድ መንፈሳዊ አባት የማይጠበቅ ተግባር እየፈጸሙ ነው በሚል ከአጥቢያው ምእመናን፣ከአጥቢያ መንፈሳዊ ማኅበራት እና ከደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ተቃውሞ ገጠማቸው፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን ጠቅላይ ቤተክህነት ለአቤቱታ ሄደው አቡነ ጳውሎስን ለማነጋገር ተስኗቸው ተመለሱ ሲሆን አምስት ሰው ብቻ ወክለው እንዲልኩ ተነግሯቸው ከላኩ በኋላ፣‹‹አጣሪ ኮሚቴ ይሾማል›› መባላቸውን ምጮች ጠቁመዋል አቤቱታ አቅራቢዎቹ ግን የአባ ዕዝራን እንዲነሱላቸው እንጂ አጣሪ ኮሚቴ እንደማይፈለጉ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡በቤተክርስቲያኒቱ ተገኝተን ለማየት እንደሞከርነው፤በርካታ ምእመናን ‹‹መፍትሄ እስካልተሰጠን ድረስ አባ እዝራ ወደ ቤተክርስቲያኒቱ ገብተው ቢሮው ተጠቅመው ሕገወት ሥራ ሊሩ አይገባል በሚል››ተፈራርመው ቢሮውን ያሸጉት ሲሆን፡፡እርሳቸው ተነስተው መንፋሳዊ አባት እንዲሾምላቸውም 156 ገጽ ያለው የስምንት ሺህ ሰው ፊርማ ያለበት ሰነድ
ተመልክተናል፡፡
ተመልክተናል፡፡
ምእመናኑ እንደሚሉት አባ ዕዝራ ጉዳዩን የወጣቶች ጉዳይ ብቻ በማስመሰል፤‹‹ይህን ሥራ የሚሠሩት በእምነት ስም ብጥብጥ ለማስነሳት የሚፈልጉ ጥቂት ወጣቶች ናቸው››በማለት ለመንግሥት ሪፖርት በማድረግ ፖሊሶችን ወደ ግቢው በመላክ ፖሊሶቹ በቀጥታ ቅዳሴ ውስጥ ገብተው ሁኔታውን ለማጣራት በሚሞክሩበት ጊዜ ምእመኑ በመቋሚያ እንዳባረራቸው እና በወቅቱ ከፍተኛ ግርግር እንደተፈጠረ በመጨረሻ ለማስፈራራት ይሁን በሕጋዊ መንገድ እንደመጡ ያልታወቁ ፖሊሶች ግቢውን ለቀው መውጣታቻው ነው፡፡
የአስተዳዳሪው አለመነሳት ያማረራቸው እና ‹‹እንዲነሱል ከስድስት ጊዜ በላይ ለአዲስ አበባ አገረ ስብከት ደብዳቤ ጽፈናል የሚሉት የአጥቢያው ምእመናን፣ከአጥቢያ መንፈሳዊ ማኅበራት እና ከደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ሰኞ ታኅሣሥ 2 ቀን 2004 ዓ.ም እያንዳንዳቸው 48 ሰው በሚይዙ አምስት አውቶብሶች እና በሌሎች መኪኖች ሞልተው አቤቱታ ለማቅረብ ጠቅላይ ቤተክነት ተገኝተው የነበረ ሲሆን ወደ ጊቢው ማንም ሊያስገባቸው ስላልቻለ ቅድስተ ማርያም ቤተክርስቲያን ገብተው ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ደብዳቤ አስገብተው መመለሳቸው ታውቋል፡፡
‹‹እኛ በደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል አጥቢያ የምንገኝ ምዕመናን፣አጥቢያ የምንገኝ መንፈሳዊ ማኅበራት እንዲሁም የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ከቤተክርስቲያ ጎን በመሆን አስራት በኩራት በማውጣት በቃለአዋዲው የተደነገገውን አስተዋፅኦ ፈቅደን እና ወደን በቅዳሴ፣በሰዓታት ፣በሰርክ ጉባኤ፣በልማት በመሰታፍ እግዚአብሔር የሰጠንን ዕውቀት እና ገንዘብ በመስጠት የሚጠበቅብንን መንፈሳዊ ግዴታዎች መፈጸማችን ከዚህ በፊት የተሠሩ በርካታ የልማት ሥራዎች ምስክሮች ናቸው፡፡
እንደሚታወቀው ለአንድ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ወንጌል መስፋፋት ትልቁ ጥቅሙ በሥነምግባር የታነጸ እግዚአብሔርን ፈሪ ሽማግሌ አክባሪ አገር እና ሥራ ወዳድ ትውልድ ለማፍራት ብሎም በሰላም በፍቅር እና በመቻቻል የምንኖርባትን ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚረዳ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡እንዳለመታደል ሆኖ ይህንን ኃይማኖታዊ እና አገራዊ ሓላፊነት እንዲወጡ ቤተክርስቲያን አደራ የጣለባቸው አባ ዕዝራ ተክለጊዮርጊስ ዓላማቸውን ወደ ጎን በመተው ኢሥነምግባራዊ የሆኑ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡በዚህም፡-
1.ቤተክርስቲያን የምታካሂዳቸውን የልማት እንቅስቃሴ በሚገባው ፍጥነት እንዲካሄድ ተገቢውን ክትትል አለማድረግ ይልቁንም የልማት እንቅፋት ሆኖ መገኘት
2.ለቤተክርስቲያን በውርስ፣ በስጦታ የሚገቡ ንብረቶች በቀደመው ጊዜ እንደሚደረገው ግልጽ ጨረታ ወጥቶ መከናወን ሲገባው ጥቂቶችን ብቻ ተጠቃሚ ለማድረግ ይመስላል እየተድበሰበሰ ማለፉ፡፡
3.የቀደሙትን አባቶቻችንን እና እናቶቻችንን አንጀታቸውን አጥፈው ብርድ አና ጸሐይ ሳይፈሩ የሰው ፊት ሳያፍሩ በሠሩት ታላቅ ቤተክርስቲያን መስታወት ቢሰበር ብለው በአርቆ አሳቢነት እንደ መለዋወጫ ያስቀመጡት ከውጭ የመጣ ውድ መስታወት ሕዝበ ክርስቲያኑ ሳያውቀውና ሳይነገረው ከግቢ ጠፍቷል በዚህም አስተዳዳሪው ምንም ዐይነት ርምጃ አልወሰዱም፡፡
4.የቤተክርስቲያኑ ዋና በሮች በአዲስ የተቀየሩ ሲሆን ከተነሱት በሮች መካካል አንዱ ብቻ ለትምህርት ቤቱ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ቀሪዎቹ የት እንደደረሱ በግልጽ አይታወቅም ነገር ግን ቤተክርስቲያኗን እያስተዳደረ ያለው አካል በምን አገባኝነት ይመስላል ዝምታን መርጧል፡፡
5.በመስከረም 28 ቀን 2004 ዓ.ም አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም በምእመኑና ከሐገረ ስብከት ከመጡ አካላት ጋራ ውይይት ሲደረግ ከአንድ ግለሰብ ጋራ በተፈጠረው አለመግባባት እንደ ልጅነቱ ይቅርታ ሲጠይቃቸው ከአንድ መንፈሳዊ አባት የማይጠበቅ ‹‹ይቅርታ አላደርግልህም ወግድ ከፊቴ አልባርክህም›› ማለታቸው ምእመኑ በአባትነታቸው ላይ ጥያቄ እንዲያነሳ ተገዷል
6.ከላይ የተጠቀሰው እንዳለ ሆኖ በ26/02/2004 ዓ.ም የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት የተደረገው ሰላማዊ ምርጫ ላይ ሕዝቡን በጸሎት እንዲባርኩ ሲጠየቁ የንቀት ይመስላል ከአንድ መንፈሳዊ አባት የማይጠበቅ የሚያስተዳድሩትን ሕዝብ አልባርክም ወይም አልፈታም ማለታቸው ለትዝብት ዳርጓቸዋል ለዚህም የድምጽ እና የምስል ማስረጃዎች በእጃችን ይገኛል በቀኑ የተገኘው ሕዝበ ክርስቲያን አዝኖ እና አፍሮ ተመልሷል
7.ቤተክርስቲያን እና መንግሥት ወጣቶች በአገር ግንባታ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽዕኦ ይኖራቸዋል ብለው ማበረታቻ በሚያደርጉበት በዚህ ሰዓት የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ አባ ዕዝራ ግን ‹፣እናንተ ወጣቶች ሳትበስሉ ያረራችሁ፣ኩታሮች፣እንደሞፈር መነደል ይገባችኋል፣ሰይፍ ይመዘዝባችኋል›. እና ሌሎች ከመንፈሳዊ ሰው የማጠበቁ ያልታረሙ አጸያፊ ቃላትን በመጠቀም ምእመኑን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ወይንም ግጭት እንዲገፋፋ እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ ‹‹የመከበር መብት ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ ነው›.
8.የሕዳር ሚካኤል ገቢ እጅግ ብዙ መሆኑ እየታወቀ ሰበካ ጉባኤ በሌለበት ቆጠራ አካሂደዋል ይህ ደግሞ የቤተ ክርስቲየንን ንብረት ለብክነት ብሎም ለምዝበራ እንዲጋለጥ ያደርጋል በዚህ መካካል ለሚባክኑት እና ለባከኑት ንብረቶች ተጠያቂው አስተዳዳሪው እና አስተዳዳሪው መሆኑን እንገልጻለን፡፡
9.በቁጥር ደ/መ/ቅ/ሚ/ሰ/ት ቤት 019/2004 በቀን ኅዳር 09/2004 ዓ.ም ለአዲስ አበባ አገረ ስብከት በጻፍነው የእግድ ደብዳቤ የቆጠራ ሂደቱ እንዲታገድልን አሊያም ገለልተኛ አካላት እንዲቋቋም ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም ስለዚህ ችግሩ እየሰፋ መሆኑን የሚመለከተው ሁሉ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን፡፡
10.በኅዳር 13 ቀን 2004 ዓ.ም ቀድመን ያስገባናቸውን ደብዳቤዎች ምክንያት አድርገን ለሚመለከተው ሁሉ ጥያቄዎቻንን ያቀረብን ሲሆን በቂ ምላሽ ባለማግኘታችን የሚገባውን አማራጭ ለመጠቀም ተገደናል፡፡
እንግዲህ ቅዱስ አባታችን ይህንን እና ሌሎች በጹሑፍ ልንገልጻቸው የከበዱንን ከክርስቲያናዊ የሞራል አስተምህሮ ያፈነገጡ ስድብ እና ንቀቶችን መታገሳችን መንፈሳዊነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ለመክፈል እና ቅድሱነቶን በማክበር ሲሆን ከሚገባው በላይ ማዘናችን ለምሬት ዳርጎናል እና ከዚህ በኋላ የእርሳቸውን አባትነት የማንፈልገው እና የማቀበለው መሆናችንን እየገለጽን ይህ ደብዳቤ ከገባባት ከኅዳር 13/2004 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ አምስት ቀናት ውስጥ እንዲነሱልን እየጠየቅን በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ጥያቄያችን ምላሽ የማያገኝ ከሆነ የራሳችንን ርምጃ የምንወስድ መሆናችንን እንገልጻለን፡፡››
ይህን ከላይ የተጠቀሰውን ደብዳቤ ካስገቡ በኋላ ታኅሣሥ 5 ቀን 2004 ዓ.ም አምስት ተወካዮች ፓትርያርኩ ጋር ቀርበው የተነጋገሩ ሲሆን፣‹‹አጣሪ ኮሚቴ መድበን ጉዳዩ እንዲጣራ እናደርጋለን›› ብለው እንደመለሱዋቸው ታውቋል፡፡
No comments:
Post a Comment