(ኖላዊ ዘተዋሕዶ፤ሕዳር 28 ፤2004)፡- በአንድ ወቅት አዲስ አበባ የሚገኘውን ጊዮን ሆቴል ሊገዙ እንደሆነ የተነገረላቸው የግርማዊ ቀዳማዊ ዐጼ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ እንደሚሠሩት ስለገለጹላቸው ብቻ ከማንም ጋር ሳይመካከሩ 350 ሚሊዮን ብር በሚደርስ ከፍተኛ ወጪ እንዲሠራ በአክሱም ከተማ ያስጀመሩት ሙዚየም ግንባታ ሁለተኛ ክፍያ ፤የአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት፣ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት እና የጠቅላይ ቤተክህነት ሠራተኞች ከየትም ብለው አፈላልገው እንዲሰጡ ለሓላፊዎች ተነገራቸው፡፡ አድባራቱ የሚፈለግባቸውን 20 በመቶ ገቢ እንዲያስገቡ ተጠይቀዋል፡፡ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት በክፍለ ከተሞች ልክ በ10 ተከፍሎ ይተዳደራል ተብሏል፡፡
ምንጮች እንደጠቆሙት፤ የግርማዊ ቀዳማዊ ዐጼ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ ሙዚየሙን ለመሥራት ቃል ከገባ እና ፓትርያርኩም ግንባታው ከ8 እስከ 9 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሰራ ያለ ጨረታ ለተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ከሰጡ በኋላ ቃል የገባው ግለሰብ ሊያገኙት እንዳልቻሉ ነው፡፡ ፓትርያርኩ በስሜት ተነሳስተው ጥናት ላልተደረገበት ፕሮጀክት 16 ሚሊዮን ብር ቅድሚያ ክፍያ የከፈሉ ሲሆን ኮንትራክተሩ ሁለተኛው ክፍያ እንዲከፈለው አስጨንቆ እንደያዛቸው ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
ምንጮቹ እንደሚሉት ኮንትራክተሩ በተሰጠው ቅድሚያ ክፍያ የመጀመሪያ ደረጃ ቁፋሮ ቢያከናውንም ሁለተኛው ክፍያ ተፈጽሞለት ኮንክሪት መሙላት ካልጀመረ በመጪው ክረምት የሚጥለው ዝናብ የዱሮውን ቤተክርስቲያን ጠራርጎ ይዞት ሊሄድ ይችላል ከሚል ስጋት መሆኑ ታውቋል፡፡ቤተክርስቲያኒቱ በአክሱም ከተማ አዲስ ለማስገንባት ያሰበችውን ሙዚየም በሚመለከት እርዳታ እንዲሰጥ የተጠየቀው ዪኒስኮ በቦታው ላይ ምንም ዐይነት ቅርስ እንደሌለ ድምዳሜ ላይ ሊያደርሰው የሚችለውን ጥናት አጠናቆ ካልጨረሰ እርዳታ እንደማይለግስ ገልጾ ጥናቱን እስኪያጠናቅቅ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ እንደነበር ታውቋል፡፡ሌሎች ለጋሾችም የዩኒስኮን ውጤት ሰምተው እርዳታ እንደሚሰጡ አስታውቀው ነበረ ቢሆንም ፓትራያርኩ በችኮላ በወሰኑት ውሳኔ ራሳቸው አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ኅዳር 26 ቀን 2003 ዓ.ም በአዲስ አበባ አገረ ስብከት ሥር የሚገኙ ገዳማት አስተዳዳሪዎችን ሰብስበው ያነጋገሩት አዲሱ የአገረ ስብከቱ ሥራ አሥኪያጅ አቡነ ኤልያስ፤ ‹‹ስብሰባው የተዘጋጀው ለትውውቅ፣ እያንዳንዱ ደብር ለአገረ ስብከቱ ማስገባት የሚጠበቅበትን 20 በመቶ ድርሻ እንድታስገቡ ለማሳሳብ እና ለአክሱም ሙዚየም ገንዘብ እንድታዋጡ ነው›› እንዳሏቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ አቡነ ኤልያስ ለተሰብሳቢዎቹ እንደገለጹላቸው ‹‹አባታችን ሁለተኛ ክፍያውን እንዲፈጽሙ ኮንትራክተሩ ፈትሮ ይዟቸዋል፡፡ እሳቸውም እኔን ውለድ ያሉኝ ከመሄዳቸው በፊት ነበር መጀመሪያ 15 ሚሊዮን ብር እንዳሰባስብ ነበር የተፈለገው በኋላ ግን 11 ሚሊዮን ብርም ቢሆን ይበቃኛል እሱን ይዤ መሄድ አለብኝ ብለውኝ ነበር ነገር ግን እናንተም ገንዘቡን መስጠት አልቻላችሁም አለበለዚያ እያንዳንዱ ሰው የአንድ ወር ደምወዙን ለመስጠት ቃል ግባና ደብሮቹ ከተቀማጭ ላይ አንስታችሁ ገቢ አድርጉ›› ብለዋቸዋል፡፡
አስተዳዳሪዎቹ በበኩላቸው በቅርቡ ቤተክህነት ለሠራተኞቹ ባደረገችው በጥናት ላይ ያልተመሰረተ የደሞዝ ጭማሪ ለአንድ ሠራተኛ በአንድ ጊዜ ከ1000 ብር ጀምሮ ጭማሪ መደረጉን እና ጭማሪውም ከጥር ወር ጀምሮ ታስቦ ይሰጣቸው የሚል ትእዛዝ በመተላለፉ ሁሉም ደብር ካዝናውን አሟጦ መክፈሉን እና ገንዘብ ያለው አንድም ደብር እንደሌለ በመግለጽ አንዳንድ ሓላፊዎች አስተያየት ሰጥተው እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ቀደም ሲልም የአክሱም ሙዚየም ማሰሪያ የሚል የገቢ ማሰባሰቢያ ሳጥን በትልልቅ አድባራት ተቀምጦ 2 ሚሊዮን የማይሞላ ብር መሰብሰቡን በመጠቆም በምን ተአምር ነው ገዳማቱ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ ሊያዋጡ የሚችሉት በማለት በስብሰባው ተካፍለው የነበሩት አስተያየት ሰጪ ይናገራሉ፡፡
በሌላ በኩል ፓትርያርኩ በአክሱም ጽዮን በመሠራት ላይ ያለውን ሙዚየም በከተማው ተገኝተው ከጎበኙ በኋላ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጥንታዊ ቅርሶች ሕልውናና ደህንነት ትኩረት በመስጠት በዘመናዊ ሙዚየም ተሰባስበው የሚቀመጡበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባዋል፡፡›› ብለዋል:: ግንባታው 17 በመቶ መጠናቀቁን እና ለአጠቃላይ ወጪው ሕዝቡ እንዲረባረብ ጠይቀዋል፡፡ የግንባታውን መሠራት የሚደግፉት ምንጮቹ በጥናት ላይ ሳይመሰረት ተጀምሮ መጨረሻው አድባራትን ማስጨነቁ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡
መልካሙን ያሳየን፣
No comments:
Post a Comment