Tuesday, December 6, 2011

ኖላዊ  ዘተዋሕዶ  ማን ነዉ?
                              
                                           ኖላዊ  ዘተዋሕዶ 
ኖላዊ  ዘተዋሕዶ ማለት የተዋሕዶ እረኛ ማለት ነው።ተዋሕዶ ሃይማኖት እረኛዋ ጠባቂዋ ቤዛ ኲሉ ዓለም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ተዋሕዶ ሃይማኖት ነቅዕ ንጹሕ (የጠራ ምንጭ) ናት።ከጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባቶቻችን ሐዋርያት ኋላም ለሊቃውንት ቀጥሎም ለካህናት በአደራ የተሠጠች አንዲት ሃይማኖት ናት/ ይሁ 1-3//ኤፌ4-5/።የቅዱሳን ርስት፣የባህታውያን የጸሎት ፍሬ፣የሰማዕታት ተጋድሎ፣የምእመናን ተስፋ ናት።ስለዚህም በልዑል እግዚአብሔር ታላቅ ቸርነት የዚህች ርትዕት ሃይማኖት ልጆች በመሆናችን አንደበታችን ሁልጊዜም ፈጣሪን ያመሰግናል።
ዘመናችን ሰይጣን የሰው ልጆችን ሕይወት እንደ ስንዴ ለማበጠር በውስጥ በአፍአ ፈተና ያበዛበት ዘመን ነው/ሉቃ 22-31/። ይህችህን ቅድስት ሃይማኖት ለማወክ ማዕበል በየአቅጣጫው አስነስቶ የምናይበት ነው።እንዲህ  ባለው የፈተና ወቅት ማንቀላፋት ተገቢ እንዳልሆነ እናምናለን።በመንፈሳዊ ሕይወታችን ከሌላው የተሻልን እንደሆንን ራሳችንን ባንቆጥርም በቤተክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰው ያለው ሁኔታ ግን ያሳስበናል።አይተን እንዳላየን እንዳንሆንም የቅዱሳን አበው የአደራ ቃል ግድ ይለናል።
 የቤተክነታችን የተበላሸ  አሠራር፣የሐሰተኛ ወንድሞች አጋጣሚውን ለመጠቀም መሞከር፣የ”ተሐድሶ”የግብር አባቶች የሆኑ የሉተራውያን ተንኰል፣የመሐመዳውያን ዓይን ያወጣ ድፍረት እነዚህ ሁሉ እንቅልፍ ነስተውናል።እግዚአብሔር ቢፈቅድ ብንኖርም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ትንሣኤ በዓይናችን እስክናይ የበኩላችንን ለማለት ብዕራችንን አንስተናል።የቤተክርሰቲያኒቱ ዶግማ፣ቀኖና ሥርዓት፣ትወፊት ተከብሮ እንዲኖር የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት በዓለም ሁሉ እንዲሰበክ፣የቅድስተ ቅዱሳን የእመቤታችን የድንግል ማርያም ክብርና አማላጅነት፣የቅዱሳን ሁሉ ክብርና አማላጅነት በትውልዱ ልቡና ከፍ ከፍ እንዳለ እንዲኖር የልጅነት ድርሻችንን ለመወጣት አሐዱ ብለናል።ከአሰብነው እንድንደርስ ወጣኒ ብቻ ሳይሆን ፈጻሚም እንድንሆን በጸሎታችሁ አትርሱን። 
“በወንዝ ፍርሃት በወንበዴዎች ፍርሃት በወገኔ በኩል ፍርሃት በአሕዛብ በኩል ፍርሃት በምድረ በዳ ፍርሃት በባሕር ፍርሃት በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍረሃት ነበረብኝ፤”/2ኛ ቆሮ 11 -26/፡፡”የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብደኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁል አሳብ ነው፡፡” /2ኛ ቆሮ 11 -28/፡፡
                                                   ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                                                                    መልካሙን ያሳየን
                                                             አሜን


 

No comments:

Post a Comment