· የመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ጽ/ቤት አይመለከተውም ተብሎ ተሰናብቷል
· የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ልማት ድርጅቱ እና ተከራዮቹ ከሆቴሉ ዞር እንዲሉ ተነግሯቸዋል
· ፓትርያርኩን የአስተዳዳሪው ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ አሜሪካ ጉዞ ጥርጣሬ ላይ ጥሏቸዋል
· በአስተዳዳሪው ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ ላይ መዛታቸውም ተሰምቷል፡፡
· ደብሩ ተከራዮቹን አስወጥቶ ሆቴሉን ተረክቧል
(ኖላዊ ዘተዋሕዶ፤ታህሳስ 1 ፤2004)፡- የግርማዊ ቀዳማዊ ዐጼ ኀይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ የሆኑት ልዕልት ኂሩት ደስታ“ለቅዱስ ላሊበላ ደብር መርጃ ይሁን” በሚል በስጦታ ያበረከቱት የ‹‹ሰባት ወይራ ሆቴል ባለቤት››የቅዱስ ላሊበላ ደብር መሆኑ በፍርድ ቤት ተረጋገጠ፡፡
የጉዳዩ መነሻ
የግርማዊ ቀዳማዊ ዐጼ ኀይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ የሆኑት ልዕልት ኂሩት ደስታ በ1963 ዓ.ም “ለቅዱስ ላሊበላ ደብር መርጃ ይሁን” በማለት ደብሩ ሆቴሉን በባለቤትነት ይዞ እያስተዳደረ ገቢው ለማስቀደሻ እና ለጧፍ እንዲጠቀምበት በማሰብ የ‹‹ሰባት ወይራ ሆቴል››ን በጹሑፍ ይሰጣሉ፡፡ ገዳሙ ስጦታውን ከተቀበለ አራት ድፍን ዓመታት እንኳን በቅጡ ሳይቆጠር በደርግ የሥልጣን ዘመን ከተወረሱት በርካታ ቤቶች መካከል አንዱ ሆነና በጊዮን ሆቴሎች አስተዳደር ድርጅት እጅ ወደቀ፡፡ኢሕአዴግ የመንግሥትነቱን ሥልጣን ከተረከበ በኋላ በ1991 ዓ.ም ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ለጠቅላይ ቤተክነት ‹‹ሰባት ወይራ›› የተባለው ሆቴል ንብረትነቱ የቅዱስ ላሊበላ ገዳም መሆኑ ስለተረጋገጠ፣ እንዲረከቡ የሚጠይቅ ደብዳቤ ይጽፋል፡፡ቤተክህነቱም ደብዳቤውን መነሻ በማድረግ ገዳሙ ሆቴሉን ለመረከብ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርግ ለደብሩ በደብዳቤ ያስታውቃል፡፡እነዚህ ደብዳቤዎች ከተጻጻፉ ከሰባት ዓመት በኋላ፣ በ1997 ዓ.ም ከገዳሙ እውቅና ውጪ በግዮን ሆቴሎች እና በጠቅላይ መካከል ርክክብ ይፈጸማል፡፡
ቤተክህነቱ
ቤተክህነቱ
የገዳሙን የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ሆቴሉ ለገዳሙ የተበረከተ ስጦታ መሆኑን በመግለጽ ሆቴሉ ለደብሩ እንዲመለስ ቢጠይቁም ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሆቴሉን እንደ ሌሎቹ የተወረሱ የቤተክርስቲያኒቱ ቤቶች ከመንግሥት ጋር በተደረገ ልዩ ስምምነት ያስመለሰችው በመሆኑ፣ ንብረትነቱ የእርሷ እንጂ የገዳሙ ሊሆን እንደማይገባ በመግለጽ ሆቴሉም መተዳደር ያለበት በጠቅላይ ቤተክህነቱ ሥር ነው ስትል ክርክር ታቀርባለች፡፡በዚህም መሰረት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የቤቶችና ሕንጻዎች አስመላሽ ኮሚቴ ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ተረክቦ ለሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት፣ ሀገረ ስብከቱም ለደብሩ ሊሰጥ ስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡
በወቅቱ
በወቅቱ
የመንግሥት ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ በ1991 ዓ.ም የሆቴሉ ንብረትነት የደብሩ መሆኑን ያረጋገጠበት ሰነድ ቢኖርም ፣የደብሩ አስተዳደርና የከተማው ምእመናን ሆቴሉ እንዲመለስላቸው ለረጅም ጊዜ አበክረው ቢጠይቁም ጥያቄያቸውን ችላ ያለው አስመላሽ ኮሚቴው ሆቴሉን ለማከራየት በ1997 ዓ.ም ጨረታ አውጥቶ ለደብሩም “የባለቤትነት” በሚል ብር 2500 ለመስጠት ይወስናል፡፡
በጨረታው መሠረት ቸሩ አበበ የተባሉ ምእመን በየወሩ ብር 32,000 የጨረታ ዋጋ በመስጠት ከፍተኛውን የኪራይ ዋጋ ቢያቀርቡም ብር 25,000 ኪራይ ላቀረቡትና የአቡነ ጳውሎስ ዘመድ ናቸው ለተባሉት ለአቶ አምኃ ኀይለ ሥላሴ ይፈቀዳል፡፡ ይህ የኪራይ ዋጋ እንደተባለው በየወሩ ለቤተ ክህነቱ መከፈሉን እንደሚጠራጠሩ የሚገልጹት ምንጮቹ፣ ለደብሩ ባለቤትነት ተብሎ የሚከፈለው ብር 2 ሺህ 500 በታኅሣሥ 2003 ዓ.ም ወደ ብር 5000 ከፍ ቢልም የተለያየ ምክንያት እየተሰጣቸው አንድም ጊዜ በወቅቱ እንዳልተከፈላቸው ምንጮች ያስረዳሉ፡፡
ክሱ እንዴት እና መቼ ተጀመረ?
የሰባት ወይራ ሆቴል በየዓመቱ በቅዱስ ላሊበላ ደብር በድምቀት በሚከበረው የልደት በዓል ወቅት ከአንድ ሚልዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚያስገኝ የሚገመት ሲሆን ሆቴሉን የተከራዩት ግለሰብ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ምንም ዓይነት ግብር ይከፍሉ ስላልነበር የከተማው የገቢዎች ጽ/ቤት ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት በአድራሻው፤ በግልባጩ ደግሞ ለላሊበላ ደብር 216,000 ብር ውዝፍ ግብር እንዲከፈለው ይጠይቃል፡፡ግብሩን ከፍለው የባለቤትነት ደብተሩን መውሰድ የፈለጉት ሁለቱም አካላት ሲሆኑ ጠቅላይ ቤተክህነት ይህንኑ እንቅስቃሴ በመጀመሩ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት አምርቶ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንቅስቃሴ ይታገዳል፡፡
የፍርድ ቤቱ ጉዳይ በእንጥልጥል እንዳለ በዓለም የቅርስ ይዞታዎች መስፈርት መሠረት “ኮር ዞን” ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ግንባታ እንዲፈርስ ወይም እንዲጸዳ የሚያዝዝ በመሆኑ በ”ኮር ዞን” ውስጥ ያረፈው ሰባት ወይራ ሆቴልም ተነሥቶ ምትክ ቦታ እንዲሰጠው ይወሰናል፡፡የአቶ አምኃ ኀይለ ሥላሴ ተወካይ ሆነው ሆቴሉን የሚያስተዳድሩት ግለሰብም ሆቴሉ ፈራሽ መሆኑን በመረዳት የሆቴሉን ጥንታዊ ዕቃዎች በአይሱዙ መኪና ጭነው በአሸተን ማርያም አቅራቢያ ወዳሠሩት ሎጅ ማጋዝ በድብቅ አጋዙ፡ከዚያም ግንቦት 26 ቀን 2003 ዓ.ም በተለየ ሁኔታ በርካታ የሆቴሉን ዕቃዎች ጭነው ሊወጡ ሲሉ የገዳሙ አባቶች እና ጠባቂዎች እጅ ከፍንጅ ይዘው ለፖሊስ አሳልፈው ይሰጧቸዋል፤ክስም ይመሰረትባቸዋል፡፡
የደብሩ አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ መኮንን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ፊርማ በተጻፈ ደብዳቤ ሰኔ 23 ቀን 2003 ዓ.ም ይጠራሉ፡፡የባለቤትነት ጥያቄውን ያነሳው ሕዝቡ መሆኑን፣ ካስፈለገ ኮሚቴው ደብዳቤ እንዲጽፍ እና ደብዳቤው በሕዝብ ፊት ተነቦ ሕዝቡ እንዲጠየቅ በማለት ቆራጥ አቋም እንዲያሳዩ ከምእመናን አደራ ተሰጥቷቸው ይላካሉ፡፡አዲስ አበባ ጠቅላይ ቤተክህነት ሲደርሱም ፓትርያርኩን እንዲያነጋግሩ ይደረጋል፡፤ፓትርያርኩም በሆቴሉ ጉዳይ ሕዝቡን እያነሳሱ መሆኑን ነግረዋቸው የተጀመረው ክስ እንዲቋረጥ እንዲያደርጉ ትእዛዝ ይሰጧቸዋል ፡፡ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ መኮንን ወደ ደብሩ ከተመለሱ በኋላ ክሱ እንዲቋረጥ የተቻላቻውን ሁሉ ጥረት ማድረጋቸውን ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቤቶችና ሕንጻዎች አስመላሽ ኮሚቴ ሊቀ መንበር መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያምም ወደ ደብሩ ሄደው በክስ መቀጠሉ ለደብሩ እንደማያዋጣ እና ከጠቅላይ ቤተክህነቱ ጋራ ተስማምተው 100,000 እንዲቀበሉ ለማግባባት ይሞክራሉ፡፡የደብሩ አስተዳደር ጽ/ቤትም በማግባቢያው ሳይታለሉ በማስፈራሪያው ሳይሸነፉ ክሱን ሳያቋርጡ እስከመጨረሻው ይከራከራሉ፡፡
ከሳሽ የቅዱስ ላሊበላ ደብር አስተዳደር፤ አንደኛ ተከሳሽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቤቶች እና ሕንጻዎች ልማት ድርጅትን ሁለተኛ ተከሳሽ ሆቴሉን የተከራዩትን አቶ አምኃ ኀይለ ሥላሴ እና ወኪላቸውን አቶ መስፍን ኀይለ ሥላሴ በማድረግ ‹‹ሰባት ወይራ ሆቴልን የቅዱስ ላሊበላ ደብር በስጦታ ያገኘው በመሆኑ የባለቤትነት መብቱም የደብሩ መሆኑን ነገር ግን ልማት ድርጅቱ ያለአግባብ ማከራየቱን እና የሆቴሉም ንብረት በድብቅ መዘረፉን በመግለጽ እንዲሁም ልማት ድርጅቱ በማይመለከተው ጉዳይ ባለቤትነት ደብተር ከከተማው አስተዳደር ላይ እየጠየቀ በመሆኑ ሁከት ይወገድልኝ››ሲል ይጠይቃል፡፡
የቤቶችና ሕንጻዎች ልማት ድርጅት በበኩሉ ደብሩ ሕጋዊ ሰውነት ስለሌለው ክስ ማቅረብ እንደማችል፣ጊዜው የቆየ ጉዳይ በመሆኑ በይርጋ እንደሚታገድ፣ሆቴሉን የሚያስተዳድረው ልማት ድርጅቱ በመሆኑ ደብሩ ሁከት ይታገድልኝ የሚል ክስ ማቅረብ እንደማይችል በመግለጽ ይከራከራል፡፡ሁለተኛ ተከሳሽ ደግሞ ከከሳሽ ጋራ የውልም ሆነ የሕግ ግንኑነት ስለሌላቸው ክስ ሊቀርብበት እንደማይገባ በመግለጽ ምላሽ ይሰጣል፡፡
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ
የግራ ቀኙን ክርክር፣ምስክር ሲያዳምጥ እና ማስረጃ ሲመረምር ቆይቶ ኅዳር 12 ቀን 2004 ዓ.ም በዳኛ መቅደስ አዳል የተሰየመው የሰሜን ወሎ ላስታ ወረዳ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ፤ሆቴሉ ይገባኛል በሚል በጣልቃ ገብ ማመልከቻ በክሱ ላይ ጣልቃ ገብቶ የነበረው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክነት‹‹በተፈጠው ሁከት ላይ የሚያገባውም ነገርም ሆነ የፈጸመው ድርጊት ስለሌለ ከጉዳዩ ተሰናብቷል፤የቤቶች እና ሕንጻዎች ልማት ድርጅት ከደብሩ ላይ በስጦታ ያገኘው ቤተክርስቲያን ለላሊበላ ከተማ አገልግሎት የጠየቀው የካርታ ይሠራልኝ ጥያቄ ልማት ድርጅቱ ከዚህ በፊት የይዞታ መብት የሌለው መሆኑን የሚያስረዳ ሲሆን ይህም ተግባሩ በስውር የተሰራ ሥራ መሆኑን የሚያሳይ ስለሆነ፣ተከራዩም ግለሰብ የተከራየውን እቃ ይዞ ሲወጣ መያዙ በማስረጀ ስለተረጋገጠ ለከሳሽ ሁከቱ ይወገድለት ብለናል››በማለት ፍርድ ቤቱ የፍርድ ውሳኔውን አስተላልፏል፡፡ተከሳሾች ውሳኔውን ፈጽመው ለኅዳር 27 ቀን እንዲቀርቡ ትእዛዝ የተሰጠ ሲሆን ምንጮች እንዳረጋገጡት በእለቱ የቤቶች እና ሕንጻዎች ልማት ድርጅት በውሳኔው ላይ ይግባኝ በማቅረቡ ችሎት ቀርቦ በፍርድ ውሳኔው መሰረት መፈጸሙን ሳያስረዳ ቀርቷል፡፡
የፍርድ ውሳኔውን ተከትሎም ደብሩ በፖሊስ እና በቀበሌ አመራሮች እማኝነት ሆቴሉን መረከቡ ታውቋል፡፡የሆቴሉ ተከራይ በአሸተን ማርያም አቅራቢያ አካባቢ ባሠሩት ሎጅ ውስጥም ፍተሻ ተደርጎ የሆቴሉ አልጋዎች መገኘታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በወቅቱ ክሱን እንዲቋረጥ እንዲያደርጉ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የነበሩት የደብሩ አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ መኮንን በአሁኑ ወቅት አሜሪካ የሚገኙ ሲሆን፤‹‹ይቺን ስለሚያውቅ ነው ለካ እዚያ የተደበቀው እንተያያታለና››በማለት ፓትርያረኩ በአባ ገብረ ኢየሱስ ላይ መዛታቸውም ተሰምቷል፡፡
No comments:
Post a Comment